የአማራ እና የትግራይ ህዝቦች የጋራ ምክክር መድረክ መካሄዱ ተገለጸ

የአማራ እና የትግራይ ህዝቦች የጋራ ምክክር መድረክ መካሄዱ ተገለጸ፡፡

"አብሮነታችን ለሰላማችን፤ ሰላማችን ለአብሮነታችን" በሚል መሪ ቃል የአማራ እና የትግራይ ህዝቦች የጋራ ምክክር መድረክ በጎንደር ከተማ ከህዳር 9-10/2010 ዓ.ም ጀምሮ መካሄዱን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ገለፁ፡፡

የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በመክፈቻ ንግግራቸው እንደተናገሩት የአማራና የትግራይ ህዝቦች ከጥንት እስከ ዛሬ በአጥንትና በደማቸው የገነቡት ኢትዩጵያዊነት ድር እና ማግ ሆኖ በአንድነት ተሳስረው ከመኖራቸው በላይ በእምነት፣ በባህልና ኗኗራቸው ብዙ የጋራ ታሪክ የገነቡ ህዝቦች ናቸው ብለዋል።

የትግራይ እና የአማራ ህዝቦች የሚያኮራ የግንኙነት ታሪክ ስናወሳ የጥንቱን ብቻ አይደለም በቅርብ ጊዜ በተካሄደው የሰላምና የዲሞክራሲ የትግል ሂደትም እነዚህ በጋራ ለህዝቦች ነፃነትና እኩልነት በአንድ ላይ ቁመው አኩሪ መስዋዕትነት ከፍለው ጨቋኙን መንግስት ገርስሠው ከመላው ኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ጋር በአንድነት አዲስ ስርዓት መስርተዋል፡፡ የእነዚህ ህዝቦች ማንነት ሲጀመርም በብዙ መልኩ የተቆራኘ ነው ፡፡ የአማራና ትግራይ ህዝቦች በመልካም ጉርብትና ለዘመናት አብረው ከመኖራቸው ባሻገር በእምነት፤ በባህል፤ በአኗኗራቸውና በአይነት ብዙ የጋራ እሴቶቻቸው ተሳስረው የጋራ ታሪክ የገነቡ ህዝቦች ናቸው በማለት ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪ ርዕሰ መስተዳድሩ እንደተናገሩት የአማራ ህዝብ ስራ ወዳድ፣ በላቡ የሚኖር፣ ሀይማኖቱን ጠባቂ፣ እንግዳ ተቀባይ፣ ነፃነቱን አፍቃሪ እና በኢትዪጵያዊነቱ የማይደራደር ህዝብ ነው። በቀጣይም ይህን እሴቱን ጠብቆ በመሄድ ከሌሎች ህዝቦች ጋር የጋራ ቤታችን ኢትዩጵያ ሰላም ፣ዴሞክራሲና ፍት የተረጋገጠባት ሀገር እንድትሆን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።


የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ አባይ ወልዱ በበኩላቸው እንደተናገሩት የአማራ እና የትግራይ ህዝቦች ከጥንት ጀምረው ለኢትዩጵያ ነፃነት በጋራ እየተፋለሙ ገናና ታሪክ ማስቀጠል የቻሉ ህዝቦች ናቸው። ይህን ታሪካዊ ትስስራቸውን ለማስቀጠል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ከመቸውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በሌላ በኩል ክቡር አቶ በረከት ስምኦን  በህዝብ ለህዝብ መድረኩ "በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ፌደራላዊ ስርዓታችን ለሀገራችን ልማት፣ ሰላም እና ዴሞክራሲ ግንባታ አስፈላጊ ነው።" በሚል ባቀረቡት የመወያያ ፅሁፍ ላይ አልፎ አልፎ በሀገራችን የተከሰቱ ግጭቶች ዋነኛ መንስኤ እድገቱን ሊሸከም የሚችል ብቃት ያለው አመራር እጦት እንጂ የፌደራሊዝም ስርዓቱ የፈጠረው ችግር እንዳልሆነ ገልፀዋል።

 

በመጨረሻም በተካሄደው የህዝብ ለህዝብ መድረክ የሁለቱም ክልል ተሳታፊዎች ጥያቄዎችን በማንሳት፣ አስተያየት በመስጠት፤ የጎንደር ከተማ አስተዳደር እና ክፍለ ከተሞች በትግራይ ክልል ለሚገኙ ከተሞች የተለያዩ የማስታወሻ ሽልማቶችን በማበርከት፣ እንዲሁም ባለ 8 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ውይይቱ ተጠናቋል፡፡

 

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ሰራተኞችና አመራሮች 10ኛውን የሰንደቅ ዓለማ ቀን በፓናል ውይይት አክብረዋል

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የርዕሰ መስተዳድር /ቤት ሰራተኞችና አመራሮች 10ኛውን የሰንደቅ ዓለማ ቀን በፓናል ውይይት አክብረዋል፡፡

በምክትል ኤጀንሲ ስራ አስኪያጅ ደረጃ የዳያስፖራና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አውላቸው ማስሬ "የኢትዮጵያ ህዝቦች ትግልና ሀገራዊ ህዳሴያችን" በሚል ርዕሰ ጉዳይ የመወያያ ጽሁፍ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በፓናል ውይይቱ የተገኙት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የርዕሰ መስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ያየህ አዲስ ሰንደቅ ዓላማ የአንድ አገር ህዝቦች የማንነት መገለጫ ሲሆን በአንድ ወቅት ከፍ ወዳለ የስልጣኔ ማማ የወጣቸው ሀገር በታሪክ አጋጣሚ በተፈጠረ አለመረጋጋት የኢኮኖሚ ድቀት የድህነት መገለጫ ሆና ቆይታለች ብለዋል፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ ከነበረችበት የቁልቁለት ጉዞ ወደ ዕድገት ማማ እየገሰገሰች ያለች ሀገር መሆን ችላለች ያሉት አቶ ያየህ አዲስ በኢኮኖሚ ዕድገት፣ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንዲሁም ብዝሃነትን በማስተናገድ በኩል በአለም አቀፍ ደረጃ ተጠቃሽ ሀገር መሆን ችላለች ሰንደቅ አላማዋም ከፍ ብሎ መውለብለብ ጀምሯል ብለዋል፡፡

አክለውም ይህን ክብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ሁሉም በተሰማራበት የስራ ዘርፍ ውጤታማ ስራ በመስራት አባቶቻችን ያስተማሩን ለሰንደቅ አላማ መስዋዕትነት መክፈል አዲሱ ትውልድ የሰንደቅ አላማን ፋይዳ እንዲረዳ በማድረግ ድህነትን በማሸነፍ ሰንደቅ አላማችን ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ማድረግ ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

 

በፓናል ውይይቱ ከተገኙት ተሳታፊዎች መካከል አቶ መርሀጽድቅ መኮነን እና አቶ ሞገስ አያሌው እንደተናገሩት ትውልዱ የአዲሲቷን ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ መርሆችና እሴቶች አንግቦ እና ሰንደቋን ጨብጦ አገሩን ቀጣይነት ወዳለው ከፍታ ማማ እያወጣት ይገኛል፤ ዋነኛ ጠላታችን የሆነውን ድህነትን ለማሸነፍ በተያያዝነው ጠንካራ ትግል የህዝቦች የአንድነት ህብረቀለም ሆና እያገለገለች ያለችውን ይህቺው ሰንደቅ ዓላማችን በመሆኗ ልንጠብቃት፣ ልንንከባከባትና አስፈላጊም ከሆነ የህይወት መስዋዕትነት ልንከፍልላት የምትገባ ቅርሳችን ናት ብለዋል፡፡

 

የአማራ ክልል አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ለህግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ፡፡

የአማራ ክልል አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግህግ ታራሚዎች ይቅርታ አደረገ፡፡

አማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት ነሐሴ 29 ቀን 2009 ዓ.ም ባካሄደው 5ኛ ዙር ሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ የ2010 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለ1 ሺህ 981 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ ማድረጉን ገለፀ

 

ይቅርታ የተደረገላቸው ታራሚዎችም የወንጀልን አስከፊነት የተገነዘቡና ከወንጀል ድርጊት ለመታረም ያላቸውን ዝግጅት በመመዘን የይቅርታ መስፈርቱን ያሟሉ ሲሆኑ፣ ወደ ህብረተሰቡ ሲቀላቀሉ ሰላማዊና አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።

 

የአማራ ክልል መንግስት ከሰሜን ሱዳን ገዳሪፍ ግዛት ጋር በንግድ፣ ልማትና በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ዙሪያ ላይ ውይይት ማካሄዱ ተገለጸ

የአማራ ክልል መንግስት ከሰሜን ሱዳን ገዳሪፍ ግዛት ጋር በንግድ፣ ልማትና በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ዙሪያ ላይ ውይይት ማካሄዱ ተገለጸ፡፡

የአማራ ክልል መንግስት ከሰሜን ሱዳን ገዳሪፍ ግዛት ዋና አስተዳዳሪ እንጂነር መርጋኒ ሳሊህ እና በዋና አስተዳዳሪው የሚመራው የሰሜን ሱዳን ገዳሪፍ ግዛት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በንግድ፣ በልማትና በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ዙሪያ ላይ በባህር ዳር ተገኝተው ውይይት ማካሔዳቸውን የአብክመ ርዕሰ መስተዳድር አሳወቀ፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በምክክር መድረኩ እንደተናገሩት የገዳሪፍ ግዛት ከፍተኛ የልዖካን ቡድን እና የአማራ ክልል አቻው ከሁለቱ ጎረቤት ሀገሮች አልፎ በዓለም አጀንዳዎች ሊመክር የሚገባው በመሆኑ በዋናዋና ጉዳዮች ላይ ግልጽና አጭር ውይይት በማድረግ ሁለቱን ቀጠናዎች የሚጠቅሙ የቀጣይ አቅጣጫዎችን ጭምር ማስቀመጥ ይገባናል ብለዋል፡፡

አቶ ገዱ አያይዘውም የሁለቱ ሀገሮች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ረጅም ጊዜ ያስቆጠረና የቆየ ወዳጅነት ያለው በመሆኑ አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ ትንንሽ ችግሮች የሁለቱም ግዛቶች አመራሮች በውይይት ሊፈቱት የሚገባ እንጅ ወደ ከፋ ነገር ሊሄድ አይችልም ብለዋል፡፡

የሰሜን ሱዳን ገዳሪፍ ግዛት ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር መርጋኒ ሳሊህ ሳይድ አህመድ በበኩላቸው ልማታችሁ ጥሩ እየሄደ መሆኑን እናደንቃለን በተለይ በአባይ ወንዝ ላይ የሚሰራው ስራ ማሳያ ነው ካሉ በኋላ በሰሜን ሱዳን ገዳሪፍ ግዛት እና በአማራ ክልል  በኩል ያለው ግንኙነት ጥሩ መሆኑን ገልጸው በትምህርት፣ በጤና፣ ነጻ ገበያ ለማቋቋም በሚኖረው የነጻ ገበያ ልውውጥ ነጻ እንዲሆን፣ ህገ- ወጥ የንግድ ልውውጥ እንዳይኖር ማንኛውም ችግር እንዳይፈጠር ተቀናጅተን እንሰራለን ብለዋል፡፡

ዋና አስተዳዳሪው አክለውም በሁለቱም አካባቢ ጥሩ የሆነ ግንኙነት ስላለ የሽርክና ማህበር ለማቋቋም እንፈልጋለን፣ በእናንተ በኩል ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልግ ካለ እንፈቅዳለን እኛ ወደ እናንተ ኢንቨስት ለማድረግ ፈቃደኛ ነን በማለት ገልጸዋል፡፡

በዋና አስተዳዳሪው የተመራው ልዑካን ቡድን የገዳሪፍ ፖሊስ አዛዥ የመከላከያ ሠራዊት ኃላፊ እና የደህንነት ኃላፊው ጀኔራል መሀመድ ጦይብ በኢትዮጵያ እየተሠሩ ያሉ ልማቶች እንዳስደሰታቸው ገልጸው፣ የሁለቱ ቀጠናዎች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ታሪካዊና በወንድማማችነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ በመሆኑም በደንበር አካባቢ በተለይ ከአርሶ አደሩ ጋር የሚያጋጥመንን አለመግባባቶች አመራሮች በግልጽ ተወያይተን አቅጣጫ አስቀምጠን ግንኙነታችን በልማትና የሁለቱን ቀጠናዎች ጥቅሞች በሚያሳድጉ ጉዳዮች ላይ መሆን አለበት ብለዋል፡፡

 


በአማራ ክልል በኩልም ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ የማዕከላዊ ጎንደር ዋና አስተዳዳሪ፣የክልሉ ግብርና፣ የባህልና ቱሪዝም፣ የአስተዳደርና ጸጥታ፣ የፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ ኃላፊዎች በምክክሩ ላይ የተገኙ ሲሆን፣ በሁለቱ ቀጠናዎች ያሉ ህዝቦች ለሚፈጠረው ችግር ሁሉ ለሚመለከተው አካል መረጃ በመስጠት በውይይት እንዲፈታ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበው፡፡

 

በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የቤት መስሪያ ቦታ አሰጣጥ ማሻሻያ ረቂቅ ላይ ውሳኔ መሰጠቱ ተገለጸ

በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የቤት መስሪያ ቦታ አሰጣጥ ማሻሻያ ረቂቅ ላይ ውሳኔ መሰጠቱ ተገለጸ፡፡

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መስተዳድር ም/ቤት 5ኛ ዙር 3ኛ አመት የስራ ዘመን ነሀሴ 19/2009 ዓ/ም ባደረገው 4ኛ መደበኛ ስብሰባ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ አሰጣጣጥ ማሻሻያ ረቂቅ መመሪያ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ መሰጠቱ ተገለጸ፡፡

ስብሰባው የተጀመረው የከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ባቀረቡት ማብራሪያ ሲሆን በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በማህበር ተደራጅተው የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ለማግኘት የሚያስችላቸው መመሪያ ቁጥር 22/2007 ዓ/ም በመስተዳድር ም/ቤቱ የወጣ ቢሆንም እስከ አሁን ድረስ ጥያቄ ያቀረቡና የመመሪያውን መስፈርት አሟልተው የተመዘገቡ ዳያስፖራዎች እንደሌሉና ለመመዝገብ ዋናው ምክንያትም በመመሪያው ላይ የተቀመጡትን የቤት አይነቶች የግንባታ ወጭ ቅድሚያ 100% በመክፈል በዝግ አካውንት በባንክ ለማስቀመጥ አቅማችንን ያገናዘበ ባለመሆኑ ይሻሻልልን የሚል ጥያቄ ያላቸው በመሆኑ ቢሮው ከዳያስፖራ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ጋር በጋራ በመነጋገር መመሪያው ላይ ማሻሻያ ተደርጎ የቀረበ መሆኑን ገልጸው ማሻሻያው በዋናነት ከክፍያና ከቦታ መጠን ጋር የተያያዘ እንደሆነ አብራርተው ማሻሻያው እንዲጸድቅላቸው ጠይቀዋል፡፡

መስተዳድር ም/ቤቱም በቀረበው ጉዳይ ላይ የተለያዩ ሀሳቦችን በማንሳት በሰፊው ከተወያየ በኋላ በወጣው መመሪያ ላይ አላሰራ ያሉ ችግሮችን ፈትሾ ማሻሻያ ማድረግ ተገቢ በመሆኑ የቀረበው በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ አሰጣጥ ማሻሻያ ረቂቅ መመሪያ በቀረበበት መልኩ ተሻሽሎ ተግባራዊ እንዲደረግ ወስኗል፡፡

 

 

 
 • «
 •  Start 
 •  Prev 
 •  1 
 •  2 
 •  3 
 •  4 
 •  5 
 •  6 
 •  7 
 •  8 
 •  9 
 •  10 
 •  Next 
 •  End 
 • »


Page 1 of 13
Content View Hits : 7620129

Comments

 • Hi! Someone in my Facebook group shared this websi...
 • A motivating discussion is definitely worth commen...
 • I constantly emailed thus web site post page to al...
 • Hi there would you mind stating which blog platfor...
 • It's perfect time to make some plans for the futur...

Latest News

Who is online

We have 32 guests online

Entertainment