የህዝብ ቅሬታ ሰሚ በደሴ ከተማ ስልጠና መሰጠቱ ተገለጸ

የህዝብ ቅሬታ ሰሚ በደሴ ከተማ ስልጠና መሰጠቱ ተገለጸ፤

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የህዝብ ቅሬታ ሰሚ የ2009 የ6 ወር እቅድ አፈጻጸምና የስራ ስልጠና ከእንባ ጠባቂ ተቋም ጋር በመተባበር 130 ለሚሆኑ ለዞንና ለወረዳ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ከተማ ስልጠና መሰጠቱን ተገለጸ፡፡

የስልጠናው ዋና ዓላማ በአሁኑ ሰዓት በአዲስ መልክ አመራሩ የተደራጀ በመሆኑ አብዛኞቹ አዲስ በመሆናቸው በተለያዩ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ላይ ግልጽ ግንዛቤ ጨብጠው ስራቸውን በትጋት፣በቅንነትና በታማኝነት ህዝባችንን እንዲያገለግሉ ግምት ውስጥ ገብቶ የሚሰጥ ስልጠና ነው በማለት ስልጠናው በይፋ የተከፈተ መሆኑን የርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ተሰማ ደምሴ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ስልጠናው ያተኮረባቸው ዋና ዋና ጉዳዮችም የ2009 የ6 ወር የእቅድ አፈጻጸም ግምገማ በስልጠናዊ መልኩ መገምገም፣ በደንብ ቁጥር 130/2007 ዓ/ም በእንባ ጠባቂ ተግባርና ኃላፊነት እንዲሁም የመገናኛንና የመረጃ ነፃነትን ለመደንገግ አዋጅ ቁጥር 590/200 ክፍል ሶስት ድንጋጌዎች ፣ በገጠር መሬት አዋጆችና መመሪያዎች ፣ በአገልግሎት አሰጣጥና ማህበራዊ ተጠያቂነት ምንነትና አስፈላጊነት አስመልክቶ የሚመለከታቸው በሙያው የሰለጠኑና ልምድ ባላቸው አመራሮች ከመጋቢት 12-18/2009 ዓ/ም ድረስ ለቅሬታ ሰሚ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ስልጠናውን በተገቢው መንገድ ሰጥተዋል፡፡

ከሰልጣኞቹ መካከል አቶ በላቸው ከደቡብ ወሎ ዞን፣ አቶ አይተነው ከሰሜን ወሎ ዞን፣ የመጡ የሰጡት አስተያየት የ2009 ዓ/ም እቅድ አፈጻጸም የተከናወኑ ልዩ ልዩ ተግባሮችን በጠንካራ ጎንም ሆነ በድክመት የታዩትን በዝርዝር የቀረበ በመሆኑ ሰልጣኙ ይህንን እንደተሞክሮ በመውሰድ በሚቀጥለው 4 ወር የበለጠ እንድንሰራ ያደርገናል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ስልጠናው በየቢሮው የመጡ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ለስራችን ግልጽ የሆነ ስልጠና የሰጡን በመሆኑ ጥሩ ግንዛቤ ጨብጠን ህዝባችንን በጥሩ ሁኔታ እንድናገለግል ያደርገናል ብለዋል፡፡

 

መጋቢት 18/2009 ዓ/ም

 

የህዝብ ቅሬታ ሰሚ በእንጅባራ ከተማ ስልጠና መሰጠቱ ተገለጸ

የህዝብ ቅሬታ ሰሚ በእንጅባራ ከተማ ስልጠና መሰጠቱ ተገለጸ፤

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የህዝብ ቅሬታ ሰሚ ከህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ጋር በመተባበር ለ109 ወንድና ለ44 ሴት በድምሩ ለ153 ለሚሆኑ ለዞን፣ለወረዳና ለከተማ አስተዳደር የህዝብ ቅሬታ ሰሚ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ስልጠና መስጠቱን አስታወቀ፡፡

የስልጠናው ዋና ዓላማ በአሁኑ ሰዓት አብዛኞቹ አመራሮችና ባለሙያዎች በአዲስ መልክ የተደራጁ በመሆናቸው  በተለያዩ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ላይ ግልጽ ግንዛቤ ጨብጠው   ህዝቦችን በትጋት፣በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል እንዲችሉ መሆኑን የክልሉ ህዝብ ቅሬታ ሰሚ ኃላፊ አቶ ሰይድ እሸቴ ገልጸዋል፡፡

ስልጠናው በዋናነት ያተኮረባቸው ጉዳዮች በከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን ልማት ቢሮ አዋጆች፣ደንቦችና መመሪያዎች ፤ የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ተግባርና ኃላፊነት ከህዝብ ቅሬታ ሰሚ ጋር ያለው ግንኙነት፤ በገጠር መሬት አዋጆች፣ደንቦችና መመሪያዎች፤ በደንብ ቁጥር 130/2007 እና በአስፈጻሚ አካላት ተግባርና ኃላፊነት እንዲሁም የመገናኛና የመረጃ ነፃነትን ለመደንገግ አዋጅ ቁጥር 590/200 ክፍል ሶስት ድንጋጌዎች እና በአገልግሎት አሰጣጥና ማህበራዊ ተጠያቂነት ምንነትና አስፈላጊነት ላይ ያተኮረ ሲሆን ከተለያዩ ተቋማት በሙያው ልምድ ባላቸው አመራሮች  ከመጋቢት 19-23/2009 ዓ/ም ድረስ  ስልጠናው በተገቢው መንገድ ተሰጥቷል፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የህዝብ ቅሬታ ሰሚ የ6 ወር የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን ገምግሟል፡፡

አንዳንድ ተሳታፊዎች በስልጠናው ላይ አስተያየት ሲሰጡ በስልጠናው ጥሩ ግንዛቤ በመጨበጣችን መመሪያንና ደንቦችን ተመርኩዘን የህዝብን ቅሬታ በምን መንገድ መፍታት እንዳለብን እድል ፈጥሮልናል ብለዋል፡፡

 

መጋቢት 25/2009 ዓ/ም

 

በስመ-ንብረት ዝውውር ክፍያ አፈጻጸም ባጋጠሙ ችግሮችላይ የመፍትሄ ሀሳብ መሰጠቱ ተገለጸ

በስመ-ንብረት ዝውውር ክፍያ አፈጻጸም ባጋጠሙ ችግሮችላይ የመፍትሄ  ሀሳብ መሰጠቱ ተገለጸ፡፡

የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት 5ኛ ዙር ሁለተኛ    አመት የስራ ዘመን ጥር 19 ቀን 2009 ዓ/ም ባካሄደው 10ኛ መደበኛ ስብሰባ    በስመ-ንብረት ዝውውር ክፍያ አፈጻጸም ባጋጠሙ ችግሮች ዙሪያ ቢሮው ባቀረበው ማሻሻያ ውሳኔ መሰጠቱን አስታወቀ፡፡

ውይይቱ የተጀመረው በህግና አስተዳድር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የፍትህ ቢሮ ሀላፊ ሲሆኑ በክልሉ ቴምብር ቀረጥ አዋጅ  ቁጥር 31/1991 አንቀጽ 3/12 ስር በልዩ ሁኔታ በጋብቻ በጋራ በተፈሩ ሀብትና ንብረቶች ስመ-ንብረት ዝውውር ላይ የባል/ሚስት ድርሻን የቴምብር ቀረጥ ክፍያን የማይመለከት መሆኑን የሚጠቅስ አንድ ንዑስ አንቀጽ ቢቀመጥ፣ ቋሚ ኮሚቴው አክሎም በከተማ ልማት ፣ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ የተሻረው መመሪያ ህጋዊ አሰራሩን ተከትሎ በመመሪያ ቢሻርና ከዚሁ ጋር ተያይዞም ስመ-ንብረት ዝውውር ሲፈጸም ሚስት/ባል ከራሱ ወይም ከራሱ ድርሻ ውጭሊኖር የሚችልን የንብረት ስመ-ንብረት ማጠቃለያን አጋጣሚ መንግስት ገቢ ማግኘት ስለአለበት ከድርሻውጭ ያለው ንብረት የሚከፈልበት መሆኑን በአዋጁም ሆነ በመመሪያው ተብራርቶ ቢቀመጥ የሚል የውሳኔ ሀሳብ ኮሚቴው ማቅረቡን ገልጸዋል፡፡

በዚህ  መሰረት ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ ባልና ሚስት ሆነው በጋብቻ በጋራ ሀብትና ንብረት አፍርተው ቆይተው በተለያዩ ምክንያቶች የባልን ወይም የሚስትን ንብረት ድርሻ በስም ለማድረግ በስመ-ንብረት ዝውውር ወቅት የሚከፈሉ የታክስና የአገልግሎት ክፍያዎች ዝውውር ተጨማሪ ጥቅም በማያገኙበት የሃብትና ንብረት ባለቤት ሆነው በቆዩ የትዳር አጋሮች በአንዳቸው ስም ተመዝግቦ በመቆየቱ ብቻ 2% የቴምብር ቀረጥ ታክስ እና 3%ደግሞ የአገልግሎት ገቢ ከንብረቱ ጠቅላላ ዋጋ ታስቦ መከፈሉ አድሏዊና ኢ-ፍትሀዊ መሆኑና ጉዳዩም በዋናነት ጫና እየፈጠረ ያለው በሴቶች የንብረት ባለቤትነት ላይ መሆኑን ጉዳዮን የፍትህ ቢሮና ህግና አስተዳድር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ካቀረበው የውሳኔ ሀሳብ የተረዳ መሆኑን ምክር ቤቱ ማስተካከያ መደረግ እንዳለበት ተስማምቷል፡፡ በመሆኑም  የሀብትና ንብረት ባለቤት ሆነው በቆዩ የትዳር አጋሮች በአንዳቸው ስም ተመዝግቦ በመቆየቱ 2% የቴምብርና ቀረጥ ታክስ እና 3%የአገልግሎት ክፍያ ከንብረቱ ጠቅላላ ዋጋ ታስቦ እንዲከፍሉ ማድረግ ፍትሃዊ ባለመሆኑ በፍችና በሞት የሚደረግ የስመ-ንብረት ዝውውር ከቀረጽ ነፃ እንዲሆን፣ከዚህ ጋር በተያያዘም፣በከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ ያወጣው መመሪያ ቁጥር 4/2006 ዓ/ም አንቀጽ 14/4 በባል ወይም በሚስት ስም የተመዘገበ ንብረት ክፍፍል ሲደረግ አንደኛው ወገን የሚያጠቃልለው ሲሆን የሚከፈለው 3% የአገልግሎት ክፍያ እንዲሻር መስተዳድር ም/ቤቱ ወስኗል፡፡

 

የዳያስፖራና ህዝብ ግንኙነት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት

 

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት 6ኛ ዓመት በዓል

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት 6 ዓመት በዓል

 

የስኬታማ ጥረታችን ሃውልት - ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ  የመሰረተ ድንጋይ በታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ የተጣለው መጋቢት 24፣ 2004 ዓ/ም ነበር።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዓባይ ላይ ቤት ሰርቶ የሀገር ሲሳይ የሚሆንበት ዘመን ያበሰረ  በመሆኑ ለዘመናት ሲቆጭና ከንፈሩን ሲመጥ ለዘለቀው ኢትዮጵያዊ ደስታን የፈጠረ፤ ለሀገራችን ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዘንድም ታላቅ ተስፋን ያጫረ ነው፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ” የሀገራችን ህዳሴ ማብሰሪያ የማንነታችን አሻራ መገለጫ ሆኖ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ “ዛሬ የትናንት ውጤት ነው” እንዲሉ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ስናነሳ ወደ አእምሯችን የሚመጣው “ባለቤቶቹ እኛ፣ መሃንዲሱ እኛው፣ ግንበኞች እኛው…” የሚለው የታላቁ መሪያችን አቶ መለስ ዜናዊ ንግግር ነው፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጋቢት 24 ቀን 2004 ዓ.ም የመሠረት ድንጋይ የማኖር ሥነ- ሥርዓትን ተከትሎ በኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ዘንድ የተንጸባረቀው ስሜት ቀስቃሽና ቆስቋሽ ሳያስፈልገው፣ ዘር፣ ሃይማኖት፣ ጾታና ዕድሜ ሳይገድበው የምንጊዜውም የማንነቱ መገለጫ በሆነው ሰንደቅ ዓላማው ደምቆ ወደየአደባባዩ የተመመው መላው ኢትዮጵያዊ “ባለቤቱ እሱ፣ መሃንዲሱ ራሱ፣ ግምበኛው እርሱ…” የመሆኑን እውነታ ምላሽ የሰጠበት ሂደትም መቼም የሚዘነጋ አይሆንም፡፡ በዚህም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ለመገንባት ያለውን ቁርጠኝነት የ“ይቻላል” ምላሹን በመስጠት ታሪክ የማይዘነጋው ተግባር አከናውኗል፡፡

እንደሚታወቀው የግድቡ ግንባታ በበርካታ ክስተቶች የተሞላ ነው። በተለይም ለዘመናት አብሮን የዘለቀው ዓባይን የመገደብ አይሞከሬነት አስተሳሰብ ያከተመበትና የ“ይቻላል” አስተሳሰብ ለውጥ የተፈጠረበት፣ በየትኛውም የዓለማችን ክፍል የሚገኝ ኢትዮጵያዊ የዜግነት ድርሻውን ለመወጣት ቃል የገባበት እንዲሁም ምላሹን የሰጠበት ፕሮጀክት መሆኑ በዓለማችን በዜጎች ገንዘብና ባለቤትነት የሚገነባ ብቸኛው ፕሮጀክት መሆኑ ከፕሮጀክቱ ክስተቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ስድስት ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ግንባታው የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለዘመናት ጥቅም ሳይሰጥ የቆየው የዓባይ ወንዝ ኢትዮጵያን ለቆ ከሚወጣበት ከሃያ እስከ አርባ ኪሎ ሜትር መካከል ላይ እየተገነባ ይገኛል፡፡

ግንባታው በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ባካበተው የሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያና በሀገር በቀሉ የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፓሬሽን አማካኝነት እየተከናወነ ሲሆን፤  የግንባታ ሥራው ሲጠናቀቅ አንድ ሺህ 780 ሜትር ርዝመትና 145 ሜትር ከፍታ እንደሚኖረው የሚነገርለት የህዳሴው ግድብ ግንባታ፤ የሲቪል ሥራ የሚከናወነው በሳሊኒ ኮንስትራክሽን፣ የኤሌክትሮ እና የሃይድሮ ሜካኒካል ሥራው በብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፓሬሽን፣ የማማከሩ ተግባር ደግሞ የጣልያንና የፈረንሳይ መሃንዲሶች ጥምር ኩባንያ አማካኝነት እየተካሄደ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይህም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አስተማማኝና ዓለም አቀፋዊ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን አስችሎታል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ከፍተኛ ተስፋ የሰነቁበት፣ የዘመናት የቁጭት እንባቸው የታበሰበት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደቱ ሥራ 56 በመቶ ደርሷል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የግድቡን ሥራ ለማፋጠን የሚያስችሉ ከ2,300 በላይ የሚሆኑ ማሽነሪዎች በስፍራው ይገኛሉ፡፡ ሃያ አራት ሰዓታት ያለማቋረጥ እየተገነባ በሚገኘው የህዳሴው ግድብ የሚገኘው የሰው ኃይል 317 የውጪ አገር ባለሙያዎች፣10,355 ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች በሥራው ላይ ተሰማርተው በከፍተኛ ሀገራዊ ስሜትና ኃላፊነት ተግባራቸውን በሀገራዊ ፍቅር ስሜት በማከናወን ላይ ናቸው፡፡ በዚህም የግንባታ ሥራው በመለዋወጫና ግብዓት ረገድ አንዳች ችግር ሳይገጥመው በተፈለገው ፍጥነት እንዲጓዝ አስችሎታል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለት የኃይል ማመንጫዎች አሉት፡፡ የኃይል ማመንጫዎቹ የሚገኙት በግድቡ የቀኝና የግራ ክፍል ሲሆን፤ ሁለቱም አስራ ስድስት ዮኒቶች ይኖሩታል፡፡ በመሆኑም አስር ዩኒቶችን ያቀፈው የቀኙ ክፍል እንዲሁም ስድስት ዩኒቶች ያሉት የበስተግራ በኩል የሚገኘው የኃይል ማመንጫ እያንዳንዱ ዩኒቶች 375 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸው ናቸው።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እየተከናወነ ያለው  የኤሌትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ግንባታ ሥራ  ሲጠናቀቅ ማከፋፈያው በሀገራችን ትልቁ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ ባለ 500 ኪሎ ቮልት የኤሌትሪክ ማከፋፈያው በሀገራችን የመጀመሪያው ትልቁ ቮልቴጅ ከመሆኑም ባሻገር የኃይል መቆራረጥን በማስገድ ረገድም ሚናው የላቀ ነው፡፡

ይህም የሀገራችን የኃይል ማከፋፈያ የዕድገት ደረጃን ማሳደግ የሚችል ይሆናል፡፡

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ  በሲቪል ሥራዎች ላይ የተሰማራው ሳሊኒ ኮንስትራክሽን የቁፋሮ፣ የአርማታ ሙሌትና ተዛማጅ ስራዎችን ለማከናወን የሚያስችል በቂ ማሽነሪዎች ያሉት ሲሆን፤ በሰዓት ሁለት ሺህ ቶን ጠጠር በሚፈጭና በሰዓት 400 ሜትር ኩዮብ በሚያመርቱ ሁለት ፕላንቶች እየታገዘ የግንባታ ሥራውን በታለመለት ሁኔታ እንዲጓዝ እያደረገ ነው፡፡ ሀገር በቀሉ የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፓሬሽን በበኩሉ የኤሌክትሮ ሚካኒካልና የሃይድሮ ሜካኒካል እንዲሁም ተዛማጅ የመቆጣጠሪያ መሣሪያዎች ዲዛይን የማድረግ፣ የመፈብረክ፣ የማምረት፣ የመትከልና ፈትሾ የማስረከብ ስራውን በተገቢው ሁኔታ በመፈጸም አመርቂ ውጤት በማስመዝገብ ላይ ይገኛል፡፡ ይህም ሀገራዊ አቅምን በማጠናከር ረገድ ትልቅ አቅም እየፈጠረ በመምጣቱ፤ በዘርፉ ለሚካሄድ የግንባታ ሥራ ራስን በመቻል ረገድ ከፍተኛ ዕድል እየፈጠረ መሆኑ በገሃድ ያሳያል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተለያዩ ሁነቶችን ተሻግሮ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ በዚህም የግንባታ ሥራውን ከጋራ ተጠቃሚነት አኳያ በመመዘን ድጋፋቸውን ያንጸባረቁ ሀገሮች የተስተዋሉበት እንዲሁም ፍትሃዊ የውኃ አጠቃቀም ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት እንዲስብ አስችሏል። በተቃራኒው ደግሞ ሥራውን ከመቃወም እስከ የማደናቀፍ ሴራ ጥንስስም ታይቶበታል፡፡ ነገር ግን መንግስትና ህዝብ በሰጡት ትኩረት የግንባታ ሥራው ላፍታም ሳይደናቀፍ በታለመለት መንገድ እየተፈጸመ አሁን በሚገኝበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ለዚህም በመላው ኢትዮጵያዊ የተፈጠረው መነሳሳትና የመንግስት የፀረ- ድህነት ትግል ቁርጠኝነት ለግንባታ ሥራው የእሰካሁኑ ጉዞ ስኬታማነት በምክንያት የሚጠቀሱ ዋና ዋና ጉዳዮች ናቸው፡፡

ሀገራዊው ቀደሚ አጀንዳ የሆነው የግድቡ ሥራ በአሁኑ ጊዜም የቅርብ ክትትል አልተለየውም፡፡ መላው የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንደ “ዓይን ብሌናቸው” የሚንከባከቡት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በየዕለቱ በርካታ ዜጎች ይጎበኙታል፡፡ ይህም በሥራው ለተሰማሩ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ዜጎች ትልቅ የሞራል ስንቅ በመሆኑ ለሥራው መፋጠን ሚናው የላቀ ሆኗል፡፡ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሥራ በርካታ ጠቀሜታዎችን ያጎናጸፈ ነው፡፡ በተለይ የስራ ዕድልን ከመፍጠር አኳያ በአሁኑ ጊዜ በስራው ላይ ከተሰማሩት ከ6 ሺህ 600 የሚበልጡ ሠራተኞች ውስጥ የውጭ ዜጎች 550 ብቻ መሆናቸው ከ6000 የሚበልጡ ኢትዮጵያውያንን የዕድሉ ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል፡፡ ይህም ሀገራዊና ግለሰባዊ ፋይዳው ምን ያህል እንደሆነ መገመቱ አያቅትም፡፡ ምክንያቱም እንደ ግለሰብ የገቢ ማስገኛ ከመሆኑ-

ባሻገር፤ የዕውቀት መቅሰሚያ መንገድ በመሆኑ የነገን ብሩህነት ማመላከት ያስችላል፡፡

በተለይም የዓለማችን ከተፈጥሮ ጋር የሚሰማማ የኃይል ፍላጎትን የሚያሟላው የሃይድሮ ኃይል ማመንጫ ግንባታ ሥራ መስፋፋት ጋር ተያይዞ በዘርፉ ተሰማርቶ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችል በመሆኑ ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡

በሌላም በኩል በሀገራችን በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ለሚገኘው የመሠረተ ልማት ግንባታ ምላሽ የሚሰጥ የሰው ኃይል መፈጠሩ ሀገራዊ ፋይዳው የላቀ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለማመን በሚያዳግት ሁኔታ እያስገመገመ ለመጣው የኢንቨስትመንት ፍሰት በቂ ምላሽ መስጠት የሚችል የኃይል አቅርቦት የሚያጎናጽፍ በመሆኑ፤ ለሀገራዊው ዕድገት ቀጣይነት ታላቅ ዋስትና እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡

የግድቡ ጠቀሜታ በዚህ ብቻ የተወሰነ አይደለም።  ከጎረቤት ሀገሮች ጋርም ኢኮኖሚያዊ ትስስራችንን ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግራል፡፡ ይህም ለአካባቢው ሀገራት የጋራ ዕድገትና አስተማማኝ ሠላም መስፈን አስተዋጽኦው የጎላ ነው፡፡ በመሆኑም በጀርባችን ላይ የተፈናጠጠው ድህነትን አሽቀንጥረን ለመጣል ለጀመርነው የፀረ-ድህነት ትግል ከግብ መድረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። እርግጥም የግድቡ ግንባታ ሥራ ፅናትና ቁርጠኝነት በተሞላበት ሁኔታ በመካሄድ ላይ መሆኑን ለሚመለከተው ሰው የሚያጎናፅፈው ሀገራዊ ኩራት ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል ከማንም የሚሰወር አይመስልኝም፡፡ አዎ! የነገዋን ኢትዮጵያ የሚያመላክተው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሥራ መሠረተ ድንጋይ ከማኖር ጀምሮ መላው ኢትዮጵያዊ የሰጠው ምላሽ ለስኬታማነቱ በር መከፈት ከፍተኛ ድርሻ እንደነበረው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡

በወቅቱ በመላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተፈጠረው መነሳሳት በተለይ ለግድቡ ግንባታ መጀመር ከፍተኛ ድርሻ የነበራቸው ታላቁ መሪያችን አቶ መለስ ዜናዊ ህልፈተ- ህይወት በኋላም “እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን” የሚል ቃል በመግባት ግለቱን ጠብቆ በመጓዝ ላይ ይገኛል፡፡ እርሳቸው እንዳሉትም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ “ባለቤቱ እኛው፣ ግንበኛውም እኛ፣ መሃንዲሱም እኛው…” በመሆን ለሀገራዊው ልማታችን ምላሽ የሚሰጠውን ግድብ ማፋጠን መቻላችን ለፀረ - ድህነት ትግሉ ከግብ መድረስ ያለንን ቁርጠኝነት የሚያመላክት ተግባር ነው፡፡

ታዲያ ለግድቡ ግንባታ ስኬታማነት እየተካሄደ ያለው ሁለንተናዊ ጥረትና መላው ኢትዮጵያዊ ዜጋ እያሳየው የሚገኘው ቁርጠኝነትና ጽናት የተሞለበት ተግባር ዋነኛው ምክንያት የግድቡን ፋይዳ የሚገነዘብ፣ የነገዋን ኢትዮጵያ አርቆ የሚመለከትና የለውጥ ኃይል በመፈጠሩ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ በመሆኑም ይህ ሀገራዊ ጥንካሬ ግለቱን ጠብቆ የሚጓዝ በመሆኑ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሥራ እንደ አጀማመሩ ሁሉ ፍጻሜውም ያማረ እንደሚሆን የሚያጠራጥር አይሆንም፡፡

እርግጥም ወልዶ መሳምንና ዘርቶ መቃምን የማይመኝ ሰው ይኖራል ተብሎ ስለማይታሰብ የታላቁ ህዳሴ ግድብ “ባለቤቶቹ እኛ፣ መሃንዲሱ እኛው፣ ግንበኞቹ…” መሆናችንን እያስመሰከርን ለመጣንለት የታላቁ ህዳሴ ግድባችን በስኬት መቋጨት የ“እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን” ቃላችንን በመጠበቅ ዛሬም እንደ ከትናንቱ በበለጠ ሁኔታ በግድቡ ዙሪያ ተሰባስበን የህዳሴያችንን ጥርጊያ መንገድ ይበልጥ መክፈት ይኖርብናል።

 

የመረጃ ምንጭ፡-የአብክመ  የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት

 

የአብክመ መስተዳድር ምክር ቤት ከክልሉ በተለያዩ ከተሞች ህብረተሰቡ ለሚያነሳቸው የመኖሪያ ቤት አቅርቦትና አሰጣጥ ችግሮችን የሚፈታ መመሪያ አዘጋጀ፣

የአብክመ መስተዳድር ምክር ቤት ከክልሉ በተለያዩ ከተሞች ህብረተሰቡ  ለሚያነሳቸው የመኖሪያ ቤት አቅርቦትና አሰጣጥ ችግሮችን የሚፈታ መመሪያ አዘጋጀ፣

ከዚህ በፊት ነባርና አዲስ የመኖሪያ ቤት ህብረት ስራ ማህበራትን የመኖሪያ ቤት ግንባታና ቦታ አቅርቦት፣አሰጣጥና ግንባታን ለመወሰን የወጣው መመሪያ ቁጥር 9/2005 ዓ.ም ላይ በአፈጻጸሙ ላይ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመፍታት እና አብዛኛውን ህብረተሰብ የቤት ባለቤት ማድረግ አስቸጋሪ መሆኑን በማመን፡-

1. በመሪና በንዑስ ማዘጋጃ ቤቶች ታዳጊ ከተሞች እስከ 250 ካ.ሜ

2. በሜትሮፖሊታንት ከተሞች እስከ 100 ካ.ሜ

3. በአነስተኛ እና በመካከለኛ ከተሞች እስከ 150 ካ.ሜ የቦታ መጠን እንዲሰጥ የቦታ አሰጣጥ መመሪያ መስተዳድር ምክር ቤቱ አውጥቷል፡፡

የዲያስፖራና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

 

ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት

 
 • «
 •  Start 
 •  Prev 
 •  1 
 •  2 
 •  3 
 •  4 
 •  5 
 •  6 
 •  7 
 •  8 
 •  9 
 •  Next 
 •  End 
 • »


Page 1 of 9
Content View Hits : 6771094

Comments

 • I enjoy the information on your web site. Much tha...
 • I enjoy the information on your web site. Much tha...
 • I enjoy the information on your web site. Much tha...
 • I enjoy the information on your web site. Much tha...
 • I am truly glad to glance at this blog posts which...

Latest News

Who is online

We have 78 guests online

Entertainment